በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ጸጋው በንግግራቸው እንደገለጹት ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተናጥል በርካታ ስራዎችን ስትሰሩ እንደነበር ይታወቃል ይሁን እና በችግሩ ልክ መፍትሄ ለመስጠት እንዲያስችል በእቅድ መመምራት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል:: ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅችም የተቋቋሙበት ዓላማ ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ መስራት ማገዝ ስለሆነ በተናጥል ከመሄድ በጋራ ሆኖ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ በተናጥል የነበረውን ስራ የምናቀናጅበት መድረክ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የተራበ ዜጋ እንዳይኖር ተረባርበን የፈረሰውን መገንባት ከቻልን ድላችንን ሙሉ እናደርገዋን ብለዋል፡፡

ይህ ጦርነት ምንም ያህል ጉዳቱ የከፋ ቢሆንም አንድ ያደረገን ፣የሰበሰበን እና ያጠናከረን ጦርነት ነው ጀግኖች ለሃገር እየተሰው ባሉበት ሁኔታ ፕሮጀክቶችንም ቢሆን አጥፈን ሃገር እንድትቀጥል፣የተራበ እንዳይኖር እና የፈረሰን መገንባት ይኖርብናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን የፈጸመውን የክህደት ተግባር ለመመከትና ኢትዬጵያን በብልጽግና ጎዳና ለማስኬድ በግንባር ሕይወቱንና አካሉን መስዋእት እያደረጉ ካሉት ከጀግኖቹ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ጎን ለጎን በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን መርዳትና መልሶ ማቋቋም አንዲሁም የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት የዜግነት ሲያልፍም የሰብዓዊነት ግዴታ ነው ብለዋል፡፡ በጦርነቱ በግፍ የተቀጠፈውን ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት መመለስ ባይቻልም የደረሰውን የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ለመመለስ የሚያስችል መጠነ ሰፊ ስራ ምናልባትም ለሃገር ሉዓላዊነት ለማዳን ከተሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ መልኩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ችግር የደረሰው የሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት በመንግስት ብቻ የሚሸፈን ሳይሆን የብዙ ባለድርሻ አካላትን ርብርብ ይፈልጋል በማለት በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከተቋቋሙለት ዓላማ መካከል የሰብዓዊ ቀውሶች ላይ ምላሽ መስጠት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይህንን ሃገራዊ ጥሪ ተቀብላችሁ በቅንነት የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ለተገኛችሁ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና አጋር ድርጅቶች በባለስልጣን መስሪያቤቱ እና በራሴ ስም በቅድምያ ስለምታደርጉት የበጎነት ስራ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከፌዴራል ብሔራዊ የአደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ተወክለው የተገኙት አቶ ቢሊየን ሙዳ አጠቃላይ በሃገሪቱ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ብሎም ከሲቪል ማህረሰብ ድጀቶች የሚጠበቅ እገዛ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታ የሲማድ ሚና በተመለከተ እንዲሁም የአማራ፣የኦሮሚያ እና አፋር ክልል ተወክለው የተገኙ ሃላፊዎች በክልሎቹ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት እና ድጋፍ የሚሹ ዘርፎች ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል:: በመድረኩ ከተገኙ 250 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል ከመቶ አርባ ሁለት ሚሊየን ብር በላይ በአይነትና በገንዘብም ቃል ተገብቷል፡፡