ይህ የተባለው ለደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል በበጎ ፍቃድ ስርጸትና አመራር ማኑዋል ላይ ማስተዋወቂያና የአቅም ግንባታ ስልጠና በተሰጠበት ወቅት ነው:: በስልጠናው የሚመለከታቸው የመንግስት ቢሮ ሃላፊዎች፣የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የተቋሙ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በውይይት መድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የበጎ ፍቃድ ስራ ትኩረት እንዲሰጠው በሁሉም ክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ለመስራት እና በተለይም የበጎ ፍቃድ ስራ የብዙ ችግሮች መፍቻ ሊሆን ስለሚችል ይህ ስልጠና ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ እንደሃገር የመፈናቀል፣የጦርነት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ሌሎች ብዙ ስብራቶች አሉብን ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህን ስብራቶች በበጎ ፍቃድ ስራ ልንጠግናቸው እንችላለን ከዚህም በተጨማሪ እንደሃገር በደንብ ከሰራንበት የበጎ ፍቃድ ስራ ውጤት የምናመጣበት ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡ የበጎ ፍቃድ ስራ እንደ ሃገር በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ለማጠንከር፣መልካም እሴቶችን ለማዳበር፣ሰላምን ለማስፈን ያለው ሃገራዊ ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በቀጣይም የበጎ ፍቃድ ስራ ወቅታዊ ሳይሆን ዘላቂ ስራ እንዲሆን ፣የሚለካ፣ፖሊሲና ህግ ያለው፣ከፌደራል እስከ ክልል በተናበበ መልኩ የሚከናወን ተግባር እንዲሆን መስራት አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግም በተቋሙ የንቅናቄ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እና የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ስልጠናውን ከወሰዱ አካላትም ከስልጠናው አንጻር ተቋማቸውን መፈተሽ እና ማስተካከያ ማድረግ፣ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት ፣ የበጎ ፍቃድ ስራን ሜንስትሪም ማድረግ መቻል ፣ህግ ማውጣትና አሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በተቋሙ ላይ ስለመጡ ሪፎርሞችና ውጤቶች እዲሁም በአዲሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 የበጎ ፍቃድ እና በጎ አድራጊነት በዓልን በሃገሪቱ እንዲጎለብት ከማድረግ አንጻር የተሰጡ ተግባርና ሃላፊነቶች እንዲሁም ከዚህ አንጻር የተከናወኑ ተግባራትን ም/ዋና ዳይሬክተሩ ለሰልጣኞች አብራርተዋል፡፡ በመጨረሻም ይህንን ፕሮግራም ላስተባበሩ አካላት እና ለቪኤስኦ /VSO/ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በመድረኩ በርካታ መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡