በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ግዜ በኢትዮጵያ ለ 17ኛ ግዜ ‹‹በስነምግባር የታነፀ ከሙስና ለፀዳች ኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል ፡፡በፕሮግራሙ ላይ የዓለምአቀፍ ሁለንተናዊ ጫናን ለመቀነስ የተጀመረውን #NO MORE ወይም በቃ ንቅናቄን ተቀላቅለዋል፡፡ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ባስተላለፉት መልዕክት ሙስና ልማትን በማዳከም የሃገርን እድገት የሚያቀጭጭ፣ ሞራልና ስነምግባር ቀውስ እንዲባባስ የሚያደርግ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ምክንያት የሆነ፣ ለፍትህ መጓደል ፣ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ለተለያዩ ከፍተኛ አላስፈላጊ ጉዳቶች የሚዳርግ ወንጀል ነው ብለዋል፡፡ ሙስና በዋናነት በማደግ ላይ ያሉ ሃገሮች ላይ ከፍተኛ ውድመት የሚያስከትል መሆኑን በመግለጽ ሃገራችን ኢትዮጵያም የዚሁ ችግር ተጠቂ ነች ይህንን ችግር ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና በሁሉም ደረጃ ሃላፊነት በመውሰድ ከሙስና የፀዳና ስነምግባር የተላበሰ ዜጋን ማፍራት ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ተቋማችንን ከዚህ ብልሹ አሰራር በማፅዳት ሞዴል የሆነ የመንግስት ተቋም ለመገንባት መስራት ላይ ነን ያሉት ሃላፊው ሁላችሁም የተቋሙ አመራሮችና ባለሞያዎች የበኩላችሁን ሃላፊነት እንድትወጡ ጥሪዬን አስተላልፋለው በማለት ተናግረዋል ፡፡ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት በዓሉን ስናከብር በተቋማችን ውስጥ መነቃቃት ፈጥረን አሁን ሃገራችን ያለችበትን ሁኔታ በመገንዘብ ከሙስና የፀዳና ስነምግባር የተላበሰ ሁላችንም ተግተን መስራት እንድንችል ሁኔታዎችን መፍጠር አለብን ብለዋል ፡፡ እንዲሁም ለቃሉና ለህሊናው ታማኝ የሆነ አመራርና ባለሙያ እንዲኖርና እንዲፈጠር እንፈልጋለን በማለት በግንባር የሃገራችንን ጠላቶች ለማጥፋት ለሚዋደቁ የህግ አስከባሪዎች ሁላችንም ደጀን ልንሆናቸው ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡ ሰነዱን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የስነምግባርና ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ትግስት አቡዬ አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡: በመጨረሻም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን #NO MORE ወይም በቃ የሚለውን ንቅናቄ በመቀላቀል ሃገራችን ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት በቃ በማለት ድምፃቸውን አሰምተዋል ፡፡