በዓለም ለ30ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ የአካል ጉዳተኞች ቀን በጅግጅጋ ከተማ ሲከበር ‹‹የአካል ጉዳተኞችን መሪነትና ተሳትፎ በማረጋገጥ ተደራሽና ዘላቂ ድህረ ኮቪድ-19 እንገንባ›› የሚል መሪ ቃል አንግቧል፡፡ በክብረ በዓሉ ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦን ጨምሮ የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት አቶ ሙስጠፌ መሀመድን ጨምሮ ፣የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ደኤታ ዶ/ር ሳህረላ አብደላ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ጂማ ዲልቦ በመልዕክታቸው እንደገለጹት አካል ጉዳተኝነት ማንኛውም ሰው ባለታሰበ ጊዜና ወቅት ሊያጋጥመው የሚችልና የአካል ጉዳትና የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የሀገርና የመላው የሰው ልጆች ጉዳይ በመሆኑ የማኅበረሰቡን ንቃተ ህሊና ከፍ ማድረግና ምቹ የሆነ የስራና የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም አገራችን አሁን ተገዳ ከገባችበት ጦርነት የተነሳ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ሊጨምር የሚችል በመሆኑ ለዚህ የሚመጥን ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ “የአካል ጉዳተኞችን መሪነትና ተሳትፎ በማረጋገጥ ተደራሽና ዘላቂ ድህረ ኮቪድ-19 ዓለም በመገንባት የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ተሳትፎ ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በክብረ በዓሉ ላይ በአካል ጉዳተኞች መብትና ተጠቃሚነት ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን የዓመቱን የበጎ አርዓያ አካል ጉዳተኛ ሽልማት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፕሬዝዳንት አቶ አባይነህ ጉጆ ከክቡር ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድና ከክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እጅ ተቀብለዋል፡፡ ቀጣዩን ዓመት የዓለም የአካል ጉዳተኞች ቀንን ለማክበር የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ሀላፊነቱን ከሶማሌ ክልል ተቀብሏል፡፡