ደም የማይሸጥ የማይለወጥ የላቀ ውድ ስጦታ ነው፡፡ ሌላ ሊተካው የሚችል ምንም ነገር የለም፤ በፋብሪካም አይመረትም፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞችም ይህን ውድ ስጦታ “ደማችን” ለመከላከያ ሰራዊታችን በሚል መሪ ቃል ለ5ኛ ጊዜ የደም ልገሳ መርሀ ግብር አካሂደዋል፡፡ አገራችን አሁን እያካሄደች ባለው የህልውና ጦርነት ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችንን ከማገዝ አንጻር ህዝባችን ከኋላ ደጀን በመሆን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ከጎኑ መሆኑን ሲያረጋግጥ ቆይቷል፤ እያረጋገጠም ይገኛል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራርና ሰራተኞችም ከመከላከያ ጎን መሆናቸውን በገንዘብ፣ በአይነት እና ደም በመለገስ ድጋፋቸውን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በደም ልገሳ መርኃግብሩ ላይ እንዳሉት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና በደም እጦት ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖች አመራሩንና ሰራተኞቹን በማስተባበር ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ይሄኛውን የደም ልገሳ ለየት የሚያደርገው ለሀገር ህልውና ዘመቻ ላይ ለሚገኙት የመከላከያ ሰራዊትና ለክልል ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚኒሻ፣ በጦርነቱ ተጎጂ ለሆኑ ወገኖቻችን እንዲሁም አካባቢያቸውን በመጠበቅ ላይ ለሚገኙ ዜጎቻችን የምናደርገው በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም እንደባለስልጣን መስሪያ ቤት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋርም ከሚያስማማን ጉዳይ አንዱ ደም በገንዘብ የማይተመን ውድ ስጦታ መሆኑ ነው፡፡ በደም ውስጥ ህይወት አለ፣ ስለዚህም ደም ስንሰጥ ህይወት እየሰጠን ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የዚህ ዘመቻ አካል ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡: እንደሚታወቀው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ከሚባል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመሆን የ21 ቀን የደም ልገሳ ንቅናቄ ማስጀመራችን ይታወሳል፡፡ ይህም የዚህ ንቅናቄ አካል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው በማለት አብራርተዋል፡፡
ለመከላከያ ሰራዊቱም የምናደርገው ድጋፍ በዚሁ ብቻ የሚቆም ባለመሆኑ የተለያዩ ድጋፎችን በዓይነትና በገንዘብ እያሰባሰብን እንገኛለን፡፡ እስካሁን ከ7 ሚልየን ብር በላይ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር በአጭር ጊዜ ማሰባሰብ ችለናል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞችና አመራሩም ደሞዛቸውን እስከመለገስ የዘለቀ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡ ድግፋችን ጦርነቱ እሰከሚጠናቀቅና ሀገራችን ሰላሟ ተመልሶ ፊቷን ወደልማቱ እስክታዞር ድረስ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ድጋፍ ማሰባሰብ እንድንችል ድጋፍ ላደረጋችሁልን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞችና አመራሮች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምስጋናው ላቅ ያለ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ላይ የታደሙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሰራተኞችና አመራሮችም በቀጣይ የአገራችን ህልውና እስኪረጋገጥና ሰላም ሰፍኖ ሀገራችን ወደልማቱ ፊቷን እስክታዞር ድረስ የማያቋርጥ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።\
የመደራጀት መብት፤ ሰብዓዊነት፤ የህብረተሰቡ የላቀ ተጠቃሚነት!!!
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን!!!
Authority for civil society organizations (ACSO)