የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ (ኮክሲ) “ለ21 ቀን የደም መስጠት ድጋፍ ለወገናችን” በሚል መሪ ቃል በኢሊሊ ሆቴል ከመንግስት አካላት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡ የባለስልጣኑ ከፍተኛ ሃላፊዎችን ጨምሮ የሰለም ሚኒስቴር ሚንስትር ደኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ሂሩት ካሳ(ዶ/ር)፣ የብሄራዊ ደም ባንክ ዋና ደይሬክተር አቶ ያረጋል ባንቲእን፣የመከላከያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮኖሬል ጌትነት አዳነ እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል፡፡ በመርሀ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዳሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ለ21 ቀን ደም መስጠት መርሀግብር ግንባር ቀደም የሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ በመንቀሳቀሱ የሚያስመሰግን ተግባር ነው ሲሉ በመግለጽ ህይወቱን ቀብድ አስይዞ የትግራይ ህዝብን ይጠብቅ የነበረው የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ በአሸባሪው ህወሐት የተፈፀመው ግፍ ታሪክ ይቅር የማይለው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለ21 ቀን የሚለገሰው ደም በጦርነት ለተጎዱ ወገኖቻችን ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን የጠቀሱት  ዋና ዳይሬክተሩ ደም የሚሰጥ ሰው የሰውን ደም በከንቱ አያፈስም በማለት ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሌሎችም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም አርአያውን ተከትለው እንደሚሰሩ እምነቴ ነው ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ሂሩት ካሳ(ዶር) በበኩላቸው የማይተካ ህይወቱን ለሚሰጠን ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ደም ለመስጠት ጥምረቱ እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ሂሩት አያያዘውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ብዙ ሀሳብ፣ብዙ ራዕይ፣ ብዙ ነገር ለመስራት የሚፈልግ ሀይል ነው ግን ለመስጋል፤ ሃገር ከሌለች ምንም ነገር የለም ፤ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቁልፍ ነች ቁልፉ ከተሰበረ አፍሪካም በውጪ ሀይል የመቀራመት እድሏ ስፊ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አገራችን ሰላም፣ፍቅር፣አንድነት ተመልሶ እንዲመጣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድነት ሀላፊነታችንን መወጣት አለብን ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ራት ብቻ ሳይሆን ለማሰብም አገር ያስፈልጋል፡፡ ሌላው በክብር እንግድነት የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ የተከበሩ ታዬ ደንደዓ እንደተናገሩት በአገራችን በግል መሮጥ ባህል ሆኖ ለመደራጀት አስቸጋሪ እንደነበር በማንሳት ጥምረቱ ግን ለሌሎች በጋር መስራት ያለው ጥቅምን በማሳየቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ሁላችንም በመደራጀት በአገራችን ላይ ከውጭም ሆነ ከውስጥ የሚመጣውም ጥቃት ለመመከት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ በመግለፅ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተደምረው ለአገራቸው በጋራ ይቆማሉ እንጂ ለገንዘበ ብለው የውጭ ጠላት መንገድን አንከተልም ስላላችሁ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ስሜት ስለሆነ በሁሉም ዘንድ ሊተገበር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡:
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከቃል በላይ በተግባር ከመከላከያ ጎን በመቆም ደጀንነቱን እየገለፀ እንደሚገኝ በመግለጽ ይህንንም አጠናክሮ መቀጠል አለበት ተብሏል፡፡ በመርሀ ግብሩ ላይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ (ኮክሲ) ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም የመጀመሪያ ዙር የደም ልገሳ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደሚጀመር እና በቀጣይ በሁሉም ክለሎችና የመንግስት ተቋማት ጋር እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

 

የመደራጀት መብት፣ ሰብዓዊነት፣ የህብረተሰቡ የላቀ ተጠቃሚነት፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት