ድርጅቱ ‹‹የድህነትን ዑደት በትምህርት እንስበር›› የሚል መሪ ቃል አንግቦ በተለምዶ ቆሼ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ ህጻናትንና ወጣቶችን የትምህርት፣ የጤና፣ የምግብና የአልባሳት፣ የመጠለያ እንዲሁም ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን በመስጠት እየደገፈ የሚገኝ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ ከተመለከቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ ትምህርትን አንዱ የድህነት መቀነሻ መሳሪያ አድርጎ መጠቀሙ ባለትልቅ ራዕይ መሆኑን የሚያመላክት ነውና ለወደፊቱም አጠናክራችሁ መቀጠል ይኖርባችኋል ሲሉ ለድርጅቱ የስራ ኃላፊዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አውት ኦፍ ዘ አሽ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በፌብሯሪ 2020 በአዲሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት አዲስ ምዝገባ አድርጎ የተቋቋመ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሲሆን በድህነት ቅነሳና በትምህርት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ድርጅቱ እየረዳቸው ላሉ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ህጻናት የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን የድርጅቱ የስራ ሃላፊዎችና የወላጅ ተወካዮች ኤጀንሲው መጥቶ እያደረገ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ ስለተመለከተ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡