የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በራስ የውስጥ አቅም የ10 ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ይህ ዕቅድ የተቋሙ ርዕይ ዋነኛ ማዕዘን የሆኑትን ጠንካራ የሲቪል ማህበራት ዘርፍ እንዲፈጠር የማድረግ፤ ብቁና ውጤታማ ኤጀንሲ የመገንባት፣ የህብረተሰቡን የሲቪክ ባህሉ የማዳበር እንዲሁም በአጠቃላይ በሲቪል ማህበራት ዘርፍ እንቅስቃሴ የህብረተሰባችንን የላቀ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራትን የበለጠ ለማሳካት በሚያስችል እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የ10 ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ እንዲዘጋጅ ለማድረግ በፈረንሳይ የልማት ትብብር /AFD/ የፋይናንስ ድጋፍ አለም አቀፍ አማካሪ በሆነው በFCG-Sweden እቅዱን የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ይህ እቅድ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተመለከተ እንደአገር የምንመራበት እቅድ መሆኑን በመረዳት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ርዕይ ካለው አገራዊ የ10 ዓመት የልማት እቅድ ጋር በተጣጣመና በተናበበ መልኩ ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ መቀረፅ ያለበት መሆኑን በውይይቱ አንስተዋል፡፡

ዕቅዱን የማዘጋጀት ሂደቱ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላትን እና ሲቪል ማህበራትን በማሳተፍ የሚከናወን መሆኑ በውይይቱ የጋራ መግባባት የተፈጠረበት ሲሆን የኤጀንሲው አመራሮችና ሰራተኞች በስፋት እየተሳተፉበት የሚዘጋጅ እቅድ እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡ በእቅድ ዝግጅቱ የኤጀንሲውን የውስጥ አቅም ለመገንባት የሚያስችል እውቀትና ልምድ ከአማካሪው ድርጅት እንደሚገኝ ተስፋ የተጣለበት ሲሆን በዚሁ አግባብም ተግባራዊ መሆን እንዲችል የኤጀንሲው የቴክኒክ ኮሚቴ እና የስትሪንግ ኮሚቴ ተደራጅቶ በቅርበት ከአማካሪው ጋር እንዲሰራ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በውይይቱ ስትራቴጂክ እቅዱ ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዬች ላይ ትኩረት በማድረግ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን አማካሪው ድርጅት ከቴክኒክ ኮሚቴው ጋር በጋራ በመሆን ለኤጀንሲው ማኔጅመንት አባላትና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፤ ከባለድርሻ አካላትና ተገልጋዮች ጋር ውይይቶችን በማድረግ ግብዓት ለመውሰድ ስራ መጀመሩም ተገልጿል፡፡
እቅዱ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የአማካሪ ድርጅቱ ባለሙያዎች እያደረጉ ለሚገኙት ያለሰለሰ ጥረት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይም በዚሁ መንገድ በመፈፀም እቅዱ ደረጃውን ጠብቆ በወቅቱ እንደሚጠናቀቅ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡ የአማካሪ ድርጅቱ ኃላፊዎ በኤጀንሲው በኩል እየተደረገ ያለውን ድጋፍና ተሳትፎ በማንሳት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም በኤጀንሲው ያሉ ባለሙያዎችና ሃላፊዎች በቀጣይ እቅዱን የመተግበር ኃላፊነት የእነርሱ መሆኑን በመገንዘብ በእቅዱ ዝግጅት በቅርበት መሳተፍ፣ አስፈላጊ መረጃዎችንና ሃሳቦችን መስጠት እንዲሁም የሚሰጡ ስልጠናዎችን በትኩረት መከታተል እንደሚገባ ተገልፆል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሚዘጋጅ ወሳኝ አገራዊ እቅድ መሆኑን በማሰብ በሂደቱ ላይ በሚገባ መሳተፍ አለባቸው ብለዋል፡፡