የሲቨቢል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አዋጅ ቁጥር 1113/2011ን መሰረት አድርገው በተዘጋጁ አምስት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ለሁለት ቀናት ከሁሉም የማህበራት ህብረቶች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ ኤጀንሲው ባለፉት ሁለት አመታት የተቋቋመበትን አዋጅ ለማስፈጸም ያስችለው ዘንድ በርካታ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ለውይይት ክፍት ያደረገ ሲሆን የዚሁ አካል የሆነ የውይይት መድረክ በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል አዘጋጅቷል፡፡

 

የውይይት መድረኩን የከፈቱት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ሴክተሩ ከነበረበት ጨለማ ወጥቶ በነጻነት ለመንቀሳቀስ በሚያስችለው ጎዳና ላይ ነው ያሉ ሲሆን ኤጀንሲውም አዋጁን ለማስፈጸም ያስችለው ዘንድ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ሰርቷል ብለዋል፡፡ አያይይውም ኤጀንሲው በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 1113/2011 አንቀጽ 89 መሰረት አዋጁን ለማስፈጸም ያስችለው ዘንድ ልዩ ልዩ መመሪያዎችን የማውጣት ስልጣን የተሰጠው መሆኑን ጠቁመው ሆኖም ግን በበርካታ ምክንያቶች በተፈለገው ጊዜ ለማጸደቅ አልተቻለም ብለዋል፡፡ ለዚህም እንደምክንያት ያነሱት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በታቀደው ጊዜ አለመመስረት መሆኑን ጠቁመው የኮቪድ በኢትዮጵያ መከሰትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ሌላው እንደምክንያት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው እንዳሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴያቸውን ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን በተላበሰ መልኩ በማድረግ በስራዎቻቸው የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የቅድሚያ አጀንዳቸው አድርገው መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡

ካሁን ቀደም አምስት ረቂቅ መመሪያዎችን አዘጋጅቶ ውይይት ካደረገ በኋላ  ለምክር ቤቱ ያቀረበ ሲሆን በተመሳሳይምእነዚህ አዲስ አምስት መመሪያዎች ውይይት ተደርጎባቸው ለምክር ቤት የሚቀርቡ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ካሁን በፊት ለውይይት የቀረቡት ረቂቅ መመሪያዎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የአስተዳድር ወጪ አፈጻጸም የወጣ ረቂቅ መመሪያ፣ ስለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሂሳብ አጣሪ፣ ስለድርጅት ንብረት ግዢ፣ ሽያጭና አወጋገድ የወጣ ረቂቅ መመሪያ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ፈንድ ለማስተዳደር የወጣ ረቂቅ መመሪያ፣ የሙያ ማህበራትን ለመደገፍና ለማስተዳደር የወጣ ረቂቅ መመሪያ እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በገቢ ማሰገኛ ስራዎች ስለሚሰማሩበት የወጣ ረቂቅ መመሪያ የሚሉ ሲሆኑ በዚህኛው ዙር ደግሞ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ምዝገባ እና አስተዳደር የወጣ ረቂቅ መመሪያ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የኦዲትና የስራ ክንውን ሪፖርት አቀራረብን ለመወሰን የወጣ ረቂቅ መመሪያ፣

በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ስለሚደረግ ክትትል፣ ቁጥጥር እና ምርመራ የወጣ ረቂቅ መመሪያ፣ ስለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መዋሀድ፣ ስለድርጅት መከፋፈል፣ መለወጥ መፍረስ እና መተዳደሪያ ደንብ ስለማረጋገጥና ስለመመዝገብ የወጣ ረቂቅ መመሪያ እንዲሁም ስለጥቅም ግጭት የወጣ ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በውይይቱ በይዘቱ፣ በዓላማው፣ እንዲሁም የቋንቋ አጠቃቀምን ጨምሮ ከተሳታፊዎች አስተያየትና ጥያቄ ተነስቶ ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የኤጀንሲው ምክትትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ኤጀንሲው በተቻለው መጠን ድርጅቶችን ለማገዝና የህብረተሰብን ተጠቃሚነትን ብሎም የሀገርን ጥቅም ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ለዚህ ደግሞ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቾች ከፍተኛ ሚና ያላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም በዚህ መድረክ የሚነሱ ሀሳቦች እንደ ግብዓት የሚወሰዱ መሆናቸውን ጠቁመው ምናልባት እንደግብዓት ያልተጠቀምናቸው ከሆነ ከነምክንያቱ የሚገለጽ ይሆናል ያሉ ሲሆን ለዚህ ፕሮግራም አስተባባሪዎችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የህግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሓርነት በበኩላቸው ውይይቱ እዚሁ የሚቀር ሳይሆን ከአባላቶቻቸው ጋር ውይይት አድርገው ሰፊ ሀሳቦችን ማካተት የሚችሉበት ሁኔታ ያለ መሆኑን ጠቁመው ህብረቶቹ አባል ድርጅቶቻቸውን አወያይተው ተጨማሪ ግብዓት ይሆናል ያሉትን ከሰኔ 9/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባሉ 15 የስራ ቀናት በኤጀንሲው የህግ ክፍል ወይም በኤጀንሲው የኢሜይል አድራሻ መላክ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡