የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ሰሚት በሚገኘው ኤል ጂ ኮይካ ሆፕ ቲቬት ኮሌጅ (LG-KOIKA HOPE TVET COLLEGE) በመገኘት የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ አድርጓል፡፡

 

በእለቱ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦና የኤጀንሲው የምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ወርቁ በቲቬት ኮሌጁ በመገኘት የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴ ቅኝት አድርገዋል፡፡ በእለቱ ለኤጀንሲው የስራ ኃላፊዎች በካንትሪ ዳይሬክተሩ እና በባለሞያዎች በኩል ወርልድ ቱጌዘር (world together Ethiopia) ምን እየሰራ እንደሆነ ገለጻ የተደረገ ሲሆን በቲቬት ኮሌጁ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አንድ በአንድ አስቃኝተዋል፡፡

 

ዎርልድ ቱጌዘር ኢትዮጵያ (world together Ethiopia) በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2005ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀስ የቆየ እና ከ2007ዓ.ም ጀምሮ በኤጀንሲው ተመዝግቦ እየተንቀሳቀሰ ያለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ሲመሰረት የተለያዩ የህክምና ድጋፎችን ለማድረግ የተቋቋመ ቢሆንም በሂደት በትምህርት፣ በኢፍራስትራክቸር ልማት እንዲሁም በማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍ ላይ እየሰራ የሚገኝ ከአምስት በላይ አጋር ድርጅቶች ያሉት ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡

በእለቱ አቶ ዶንግሆ ኪም (Mr. Dongho Kim) የኮይካ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር እንዳሉት በተለይ ዎርልድ ቱጌዘር ኢትዮጵያ (world together Ethiopia) በሚሰራው ማህበራዊ ግልጋሎት ለኮርያ ዘማች አርበኞች ልዩ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን በአሁን ጊዜ ድርጅቱ ከ105 በላይ በተለያየ አካባቢ የሚገኙ የኮሪያ ዘማች ቤተሰቦችን እየደገፈ የሚገኝ መሆኑን አንስተው በትምህርት ሴክተሩም በኤል ጂ ኮይካ ሆፕ ቲቬት ኮሌጅ (LG-KOIKA HOPE TVET COLLEGE) በኩል በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ድርጅቱ ከሰባት በላይ ሀገራት ውስጥ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው ከነዚህ ውስጥም በኢትዮጵያ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከሌሎች ሀገሮች አንጻር ሲታይ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡

የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ የተመለከቱት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ድርጅቱ እየሰራ ባለው ነገር መደሰታቸውን ገልጸው በተለይም በሚሰጣቸው ስልጠናዎች ተማሪዎች ከትምህርቱ ባሻገር ስራ ፈጣሪና በተለይም ደግሞ በሰብዕና ግንባታ ላይ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

.