የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ከአፍሪካ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም ጋር የተለያዩ ስራዎችን በጋራ ለመስራት የስምምነት ፊርማ አደረጉ፡፡

አፍሪካ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚሰራ ድርጅት ሲሆን በኢትዮጵያ በህጻናትና ሰብዓዊ መብት ላይ ተመዝግቦ ለመስራት በቀድሞ አዋጅ 621/2001 በመንግስት በኩል ብዙ ችግሮች ያሳለፈ ድርጅት ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ሁኔታ ተመዝግቦ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ወ/ሮ ሳራ ገብረየስ ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ ሳራ አክለውም አፍሪካ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም በአዋጅ 1113/2011 መሰረት ዳግም ተመዝግቦ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ በመግለጽ የሚሰራቸውም ስራዎች በዋናነት በህጻናት መብት ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥናቶችንና ፖሊሲዎችን በማጥናትና በማዘገጀት ለመንግስት የሚጠቅሙ ግብአቶችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ሌላው ያነሱልን በአፍሪካ የሚታዩ የህጻናት ሰብዓዊ ችግሮች መፈታት ያለባቸው በአፍሪካውያን እንጂ በሌላ በማንም ሊሆን እንደማይችል ገልፀዋል፡፡

የአፍሪካ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ጁሀን እንዳሉት ከኤጀንሲው ጋር በአፍሪካ ቻይልድ ፖሊሲ መድረክ መካከል ያደረግነው ውይይት እና ድርድር በጣም ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም ከአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያን የመረጥንበት ዋና ምክንያቶች ኢትዮጵያ የብዙ ሺ ዘመን ታሪክ ያላትና የአለም አቀፍ ዲፕሎማት መቀመጫ በመሆኗ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም በኢትዮጵያ እንዲሁም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ባለፉት ሶስት ዓመታት  በጣም ትልቅ ለውጥ ማየታችንን እጅግ የሚደነቅ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በስምምነቱ ላይ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዳሉት የቀድሞ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ 621/2001 በድርጅቶችና በማህበራት ላይ ከፍተኛ ጫናና እንቅስቃሴያቸውን የገደበ እንደነበር በማንሳት አዲሱ አዋጅ 1113/2011 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራቸውን በሚገባ እንዲሰሩ በፈለጉት ዓላማ ላይ እንዲንቀሳቀሱ ያደረገ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም አዋጅ 1113/2011 በልዩ ሁኔታ ለህጻናት፣ ለአረጋውያን እና ለሴቶች ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች ዋንኞቹ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ኤጀንሲው በማንኛውም ጉዳዩች ላይ ለፎረሙ ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ከውጭና ከአገር ውስጥ ድርጅቶች ጋር ስራዎች የተሳለጡ እንዲሆኑና ለህብረተሰቡ የላቀ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሮ ስምምነቶችን እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡