በስምምነቱ ላይ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። ዛሬ በተደረገው ስምምነት ላይ የሶስቱ ተቋማት የስራ ሃላፊዎችም ስለ ስምምነቱ አስፈላጊነት ብሎም በቀጣይ በጋራ ስለሚሰሯቸው ጉዳዮች ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል። የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ርዕሰ አካዳሚ ዛዲግ አብርሃ፤ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት ለማሳለጥ ብቁ የሆነ አመራርን ማፍራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። አካዳሚው በተለያዩ የስራ መስኮች ብቁ እና ጠንካራ አመራሮችን ለማፍራት ከተለያዩ አካላቶች እና ተቋማቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የስምምነቱ ዋና ዓላማ በሀገሪቱ የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራሮችን አቅም ማጎልበት ብሎም በዘርፉ አርአያ እንዲሆኑ ማብቃት መሆኑን አንስተዋል። ርዕሰ-አካዳሚው ዛዲግ አክለውም የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ብሎም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጠንካራ አመራር ማፍራት ላይ በጋራ የምንሰራቸውን ስራዎች አጠናክረን መሄድ ይጠበቅብናል ብለዋል። በሀገሪቱ ጠንካራ እና ብቁ የሆነ አመራርን ማፍራት ስንችል የኢትዮጵያን ብልጽግና በፍጥነት ማረጋገጥ እንችላለን ነው ያሉት ።

May be an image of 5 people, dais and text

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት የሪፎርም ማሻሻያዎች ካደረገባቸው የስራ ዘርፎች አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ እንደሆነ ጠቁመዋል። በተደረገው የሪፎርም ማሻሻያም ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምቹ የስራ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል። ይሁን እንጂ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሀገሪቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ቢያከናውኑም ካላቸው አቅም አንጻር ያበረከቱት ሚና በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም ድርጅቶቹ ያላቸውን አቅም በሚገባ ተጠቅመው አለመስራት ፣ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ተቋም አለመገንባት መሆኑን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ለተቋቋሙለት ዓላማ አበክሮ ያለመስራትና የፋይናንስ ችግራቸውን ለመፍታት የሚያስችላቸውን አቅም አለመፍጠር እንደሆነ አብራርተዋል። እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት ብቁ የሆኑ አመራሮች በዘርፉ ማፍራት ተገቢ መሆኑን አንስተው ይህንንም ለማድረግ የሚያግዝ ፊርማ ዛሬ ተፈራርመናል ብለዋል። የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አህመድ ሁሴን በበኩላቸው በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥና የሀገርና የህዝብ ችግሮችን ለመፍታት ተቋማቶች በጋራ ተቀናጅተን መስራት የሚጠይቅበት ወቅት ነው ብለዋል። በመሆኑም የስምምነት ፊርማው እንደ ሀገር ተጨባጭ እድገትን ለማምጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ እውን ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።