ስለ ኢ.ፌ.ድ.ሪ. የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 የተቋቋመ የሕግ ሰውነት ያለው የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤት ነው፡፡


በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥትና ኢትዮጵያ ፈርማ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት የመደራጀት መብት በተሟላ ሁኔታ እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፤


ድርጅቶች በተመዘገቡበት ዓላማ መሠረት ሥራቸውን ማከናወናቸውን በመከታተልና በመቆጣጠር የሕብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤


ድርጅቶች አቅማቸው እንዲጎለብትና ተልዕኮአቸውን በብቃት እንዲወጡ ማስቻል፤


በኅብረተሰቡ ዘንድ የበጎ አድራጎት እና በጎ ፈቃደኝነት ባሕል እንዲዳብር ማድረግ፤


ድርጅቶች አሳታፊ የሆነ፣ ግልጽነትና እና ተጠያቂነት የሠፈነበት የውስጥ አስተዳደር እና አሰራር እንዲኖራቸው ማበረታታትና መደገፍ፤


በድርጅቶችና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባውን መልካም የሥራ ግንኙነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ አሰራሮችን መዘርጋት፤


ለድርጅቶች የራስ ቁጥጥርና አስተዳደር ስርዓት ተገቢውን ድጋፍ መስጠት፡፡

ታሪካዊ ዳራ

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሀገራችን ከ60 ዓመታት በፊት መታየት እንደጀመሩ አንዳንድ ሰነዶች ይገልፃሉ፡፡ በንጉሰ ነገስቱ ዘመነ መንግስት የሀገር ግዛት ሚኒስቴር እየተባለ ይጠራ የነበረው የመንግስት ተቋም ማህበራትንና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን  ከ1952-1967 ዓ.ም በፍትሃብሄር ህጉና በደንብ ቁጥር 321/1959 መሰረት ሲመዘግብ የነበረ ስለሆኑ አንዳንድ የታሪክ ድርሰናታ ያመለክታሉ፡፡ የመንግስት አስተዳደርን ከንጉሱ የተረከበረው የደርግ መንግስት ስልጣን ከያዘ በኋላ የመደራጀት መብት በመታገዱ ምዝገባ የማከናወን ስራ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ ነበረ፡፡ ይሁንና ከእርዳታና ከህፃናት ጉዳይ ጋር ብቻ በተገናኘ የቀድሞ ድርቅ ኮሚሽን በኋላም የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን እና የሕፃናት ኮሚሽን ለሀገር በቀልና ለውጭ ድርጅቶች እውቅና ይሰጡ ነበር፡፡

ከ1967 ዓ.ም እስከ ደርግ የስልጣን ዘመን መጨረሻ 1983 ዓ.ም ድረስ ተመዝግቦ የምዝገባ ወረቀት የወሰደ መንግስታዊ ያልሆነ ሀገር በቀልም ሆነ የውጭ ድርጅት የለም፡፡ ሆኖም በ1977 ዓ.ም የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የተወሰኑ የውጭ ድርጅቶች ከእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ጋር አጠቃላይ ስምምነት ተፈራርመው ይሰሩ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ድርጅቶቹ ስምምነቱን ከመፈራረማቸው በፊት ከመጡበት ሃገር በመንግስት አካል የተሰጣቸው የምስክር ወረቀትና ማቋቋሚያ ሰነድ ማቅረብ ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን በወቅቱ የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ድርጅቶቹን ለመመዝገብ በህግ የተሰጠው ስልጣን አልነበረም፡፡

የደርግ ሥርዓት በ1983 ዓ.ም ወድቆ ኢሕአዴግ የሀገሪቱን ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ የመደራጀት መብት በመፈቀዱ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ዜጎች ለመደራጀት ችለዋል፡፡ በተያያዘም የድርጅቶቹ ሚና በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች እለት ደራሽ እርዳታ ከመስጠት ባለፈ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋን መቋቋም የሚቻለው ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በማልማትና ህብረተሰቡንም ማሳተፍ በሚል አስተሳሰብ በልማት ስራ ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሰረትም ከ1983-1987 ዓ.ም ማህበራትን የመመዝገብ ስልጣንና ተግባር ሲያከናውን የቆየው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚባል መንግስተዊ ተቋም ሲሆን በ1987 ዓ.ም አስፈጻሚ አካላትን ለማቋቋ በወጣው አዋጅ ቁጥር 4/1987 የኢፌድሪ የፍትህ ሚኒስቴር የሃይማኖት ድርጅቶችን፤ አላማቸው ትርፍ ለማግኘት ያልተቋቋሙ ድርጅቶችን፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን  እና ማህበራትን የመመዝገብ ስልጣንና ተግባር በሕግ ተሰጥቶታል፡፡ በቀጣይም በአዋጅ ቁጥር 471/1998 ይሐው ማህበራትንና የሃይማት ድርጅቶችን የመመዝገብ ሥልጣን ለፍትህ ሚኒስቴር እንደተሠጠ በመቀጠሉ ፍትህ ሚኒስቴር እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ  የመመዝገብ ስራን ያከናውን ነበር፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር በ1999 ዓ.ም ባካሄደው የመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ጥናት መሰረት በዘርፉ የተመዘገበውን ዕድገት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሃይማኖት ድርጅቶች ውጭ ያሉ ማህበራትንና ዓላማቸው ለትርፍ ያልሆኑ ድርጅቶችን የመመዝገብና የማስተዳደር

ተግባር ያስችል ዘንድ አዲስ አዋጅ አዘጋጅቶ በአዋጅ ቁጥር 621/2001 “የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ” በሚል ስያሜ ራሱን የቻለ የመንግስት አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 621/2001 መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ተደራጅተው በአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት፣ ልማትና በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ በመመዝገብና ፈቃድ በመስጠት እንዲሁም በመከታተልና በመደገፍ የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚል ተልእኮ ይዞ ቢንቀሳቀስም የመደራጀትን መብት በተሟላ ሁኔታ ያላከበረና በአፈፃፀሙም በርካታ ክፍተቶች የነበረበት ስለነበረ ተልእኮውን በተገቢው የተወጣ አልነበረም፡፡ በተለይም አዋጁ የድርጅቶችና የማህበራ የእንቅስቃሴ አድማስና የገቢ ምንጭ ላይ ገደብ በመጣሉ የተነሳ ከፍተኛ ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረ አዋጅ ነበር፡፡ በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ዘርፉን የሚያስተዳድረው አዋጅ እና አፈጻመሙ ክፍተት እንዳለበት ስለታመነ አዋጅ ቁጥር 621/2001 ሙሉ በሙሉ ተሸሮ በአዲስ አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ሊተካ ችሏል፡፡ አዋጁ የድርጅቶቹንና የማህበራቱንም ስያሜ ከበጎ አድራጊነት ወደ ሲቪል ማኅበረሰብነት የቀየረና ዘርፉ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ባገናዘብ መልኩ የተቀረጸ ነው፡፡

አዲሱ አዋጅ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠውን የመደራጀት መብ ሙሉ በሙሉ ለማክበርና ተግባራዊ ለማድረግ ያለመና በዚሁ ሂደትም የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ አዋጁ በተሻረው አዋጅ ላይ የነበሩ ገደቦችን ሙሉ በሙሉ ያስቀረና የነቃና በነጻነት የተደራጀን ማኅበረሰብ የመፍጠር ዓላማ ያነገበ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሀገር ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ግንዘቤ ይወስዳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመካሄድ ላይ ባለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች /መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች/ ዘርፍ ከአራቱ የልማት ተዋንያን ማለትም ከመንግስት፤ ከግሉ ዘርፍ፤ እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘርፍ እኩል ትይዩ በመቆም ለሀገር ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳቸው በመታመኑ በሥስተኛ ረድፍ ላይ ተቀምጠው ይታያሉ፡፡

በመሆኑም የዜጎች የመደራጀት መብት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ በማድረግ የተጠያቂነት፣ ግልፀኝነትና ቀልጣፋ አሠራር በመዘርጋት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በመመዝገብና እውቅና በመስጠት እንዲሁም ድጋፋዊ ክትትል በማድረግ ህግን ተከትለው እንዲሠሩ በማብቃት በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኤጀንሲው እየሰራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በአገራችን የበጎ ፈቃድና የበጎ አድራጊነት ባህል እንዲጎለብት የሚያስችሉ ስራዎችን በተደራጀ መልኩ ለማከናወን ራሱን የቻለ የስራ ክፍል በማደራጀት በትኩረት ለመስራት ጥረቶችን እያደረገ ሲሆን ተቋሙ በህግ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በብቃት ለመወጣት እንዲያስችለው ስራዎቹን በጥናትና ምርምር በተደገፈ መልኩ እንዲሁም ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር ስትራቴጅካዊ ትብብር ለመፍጠር አስፈላጊ አደረጃጀቶችን ዘርግቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡

የባልስልጣኑ ተልዕኮ

ለመደራጀት መብት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እና ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ፤ የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን የሚያጎለብት፤ በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በሁለንተናዊ ሀገራዊ ልማት ውስጥ ጉልህ ሚና የሚጫወት፤ የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት
የሚያረጋግጥ፤ንቁና ውጤታማ የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፍ መገንባት፡፡

የባለስልጣኑ ርዕይ

የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ፤ የዳበረ የሲቪል ማህበረሰብ ተፈጥሮ ማየት

የባለስልጣኑ እሴቶች

  • አጋርነትና በቡድን መስራት፤
  • ግልፅነትና ተጠያቂነት፤
  • ታማኝነትና ርቱዕነት፤
  • ሙያዊ ብቃት፤
  • ምላሽ ሰጪነት፤
  • ሰብዓዊነት፤
  • የማያቋርጥ ለውጥ፤